Ethiopia

[email protected]
HOME NEWS PRESS CULTURE EDITORIAL ARCHIVES CONTACT US
HOME
NEWS
PRESS
CULTURE
RELIGION
ARCHIVES
MISSION
CONTACT US

LINKS
TISJD Solidarity
Abbay Media
Ethiopian News
Dagmawi
Justice in Ethiopia
Ethio Quest
MBendi
AfricaNet.com
Index on Africa
World Africa Net
Africalog

 

INT'L NEWS SITES
Africa Confidential
African Intelligence
BBC
BBC Africa
CNN
Reuters
Guardian
The Economist
The Independent
The Times
IRIN
Addis Tribune
All Africa
Walta
Focus on Africa
UNHCR

 

OPPOSITION RADIO
Radio Solidarity
German Radio
Voice of America
Nesanet
Radio UNMEE
ETV
Negat
Finote Radio
Medhin
Voice of Ethiopia

 

The Reporter: ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡-በራሳቸው ድክመት ላይም ተቃውሞ ሊያሳዩ ይገባቸዋል


Sunday, 19 July 2009

ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡-በራሳቸው ድክመት ላይም ተቃውሞ ሊያሳዩ ይገባቸዋል

አገራችን ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል፡፡ ለምርጫ ወቅት ተብሎ የሚፈጠር ጊዜያዊ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌምና በየዕለቱም የመንግሥት እንቅስቃሴን እየተከታተሉ፣ የሚወጡ ሕጎችን እየገመገሙ፣ በረቀቁት ላይ ሂስ እየሰነዘሩ መንግሥት እንዲያስተካከል፣ ካልሆነም እያጋለጡና እያሳጡ እነሱ ራሳቸው የተሻሉ በመሆናቸው ሕዝቡ አምኖ እንዲመርጣቸው የሚያደርጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡

 

በአገራችን የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ወደፊት ጠንካሮች ሊሆኑ ይችሉ እንደሁ እንጂ በአሁኑ ጊዜ ጠንካሮች አይደሉም፡፡ ብዙ የሚጎድላቸው ነገር አለ፡፡

የሚጎድላቸው ነገር የማይስተካከል ነገር አይደለም፡፡ ሊስተካከል የሚችል ነው፡፡ ይገባዋልም፡፡ ለማስተካከልና ለመስተካከል ግን ፍላጎትና ቆራጥነት እንዲሁም የአመራር ብቃት ይጠይቃል፡፡

የሚታዩት ችግሮችና የሚያስፈልጉት መፍትሔዎች እጅግ በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹን ማየትና መፈተሽ አስፈላጊና የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ችግሮቹንና መፍትሔዎችን በአጭሩ እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

1.    
የፖለቲካ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂና ስልት አልነደፉም

አንዳንድና እጅግ በጣም ውሱን ከሆኑ ተቃዋሚ ኃይሎች በቀር ሌሎቹ፣ የኢህአዴግ መንግሥትን የሚጥሉበትና ተመርጠው ሥልጣን ከያዙ ተግባር ላይ የሚያውሉት ፕሮግራም በግልፅና በአደባባይ አትመውና አሰራጭተው አይገኙም፣ አልነደፉምም፡፡ የትግል ስትራቴጂና የትግል ስልትም በግልፅ በፓርቲ ደረጃ አርቀው፣ ተወያይተው፣ አፅድቀው አይገኙም፡፡ ገዢው የኢሕአዴግ ፓርቲ ፕሮግራሜ፣ ስትራቴጂዬና ስልቴ ይኸው ብሎ ይፋ ሲያደርግ በተቃዋሚዎች በኩል ግን የለም፡፡ አንድ፣ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ ሁሉ አለን ቢሉም በአጠቃላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን የላቸውም፡፡ ይህ ስለሆነም ሥልጣን ሲይዙ፣ ኢንዱስትሪውን፣ እርሻውን፣ ትምህርቱን፣ መገናኛ ብዙሃኑን፣ ዲፕሎማሲውን፣ ወዘተ እንዴት እንደሚመሩት አይታወቅም፡፡ በአጭሩ ሲቀመጥ ግልፅ የሆነ አማራጭ ለሕዝብ አላቀረቡም ነው፡፡

ችግሩ ይህ ከሆነ መፍትሔው ግልፅ ነው፡፡ በአስቸኳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናቱን አካሂዶ፣ ጉባዔ ጠርቶ፣ በፓርቲ ደረጃ ፕሮግራም፣ ስልትና ስትራቴጂ መቅረፅ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚሰባሰበው በዚህ ዙሪያ ነውና፡፡ የምርጫው መሰረት መሆን ያለበትም ይኸው ነው፡፡

2.
ውስጠ - ፓርቲ ዴሞክራሲ የለም
በተንኮልና ጥሎ ማለፍ የተበከለ ነው

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠናክረው ለተጠናከረ የሕዝብ ዴሞክራሲ እንዲታገሉ እንጠብቃለን፡፡ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብት መስፈን ሊታገሉ የሚችሉት በውስጣቸው ዴሞክራሲ ሲኖር ሲሰፍን ነው፡፤ የውስጥና የፓርቲ መልካም አስተዳደር ፖሊሲያቸው ለሌላውና ለአገር የሚያስቀና ሲሆን ነው፡፡ የውስጥ ችግራቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድና በውይይት መፍታት ሲችሉ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ግን አይታይም፡፡ በየጊዜው ሲጣሉ፣ በየጊዜው ሲነታረኩ፣ በየጊዜው "እገሌ አይወክለንም" ሲባባሉ፣ በየጊዜው እገሌ ተባሯል ሲባል፣ እንዲያውም የታመመ አባልን ተጣልተናልና ሆስፒታል ሄዳችሁ አትጠይቁት የለም እንጠይቃለን ሲባባሉ፣ ገንዘብ ሰርቀሃል አልሰረቅኩም እያሉ ሲወነጃጀሉና ኦዲተር ገንዘብ ተበልቷል ብሎ ሲያጋልጥ   አላጋለጠም ወዘተ. ሲባል መስማት የከረመ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ይህ ጠባይና ባህርይ ወደ ሥልጣን ሲወጣ አደገኛነቱ እጥፍ ድርብ ስለሚሆን ልዩ ትኩረት በመስጠት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርቲያቸውን ዴሞክራሲያዊ ሕይወት ሊያጤኑትና ሊያጠናክሩት ይገባል፡፡

3.    
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእርስበርስ ግንኙነታቸው ሸካራ ነው

በተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለው የእርስበርስ ግንኙነት ሸካራና የጥላቻ ግንኙነት ስለሆነ ከመተባበር ሊያገኙት የሚገባቸውን ተጨማሪ ጉልበት አጥተዋል፡፡ ይህ ጉልበትና ጥናት ርቋቸዋል፡፡ በአመለካከት ሊለያዩ ይችላል፡፡ ጭፍን ድጋፍም አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን መቻቻልና የሌላውን አመለካከት ማክበር፣ መራጩ ሕዝብ በምርጫው እንዲወስን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይኸኛው ፓርቲ ከሃዲ ነው፣ ያኛው ጠላት ነው፣ ወዲያኛው አድርባይ ነው፣ እንዳትሰሙት፣ እንዳትከተሉት እያሉ ብቻ መስበክ በሳል ፖለቲከኛነትን አያመለክትም፡፡ መተባበር በሚያስፈልገው እየተለያዩ ነገር ግን በስም ብቻ አብረን ነን፣ አንድ ሆነናል ማለት ደግሞ ለማንም አይፈይድም፡፡ ያልተቀናጀ ቅንጅት መሆንን ያስከትላልና፡፡ መቻቻልና በሚያገናኝ ነጥብ ላይ መገናኘትና አብሮ መሥራት ደግሞ ብልህነትና ጉልበት ነው፡፡

4.    
የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ከአደገኛ ጠላት ጋር መርመጥመጥ ይታያል

በርግጥ ሁሉም ተቃዋሚዎች አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች የአገርን ክብርና ጥቅም አስቀድመው የአገር ጠላት የእኔም ጠላት ነው ብለው ከጠላት ጉያ ያልገቡና የሚታገሉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አስመራ ሄደው ሲሰግዱና ኢሕአዴግን ከሥልጣን አውርዳችሁ እኛን ሥልጣን ላይ አውጡን ብለው ሲማጠኑ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ መነሻውም መድረሻውም አደገኛና የጥፋትና የአገር ጠላትነት እንቅስቃሴ ነው፡፡

5.    
ከዘረኝነት፣ ጎሰኝነት፣ ጠባብ የሃይማኖት ስሜት አልፀዱም

ከኢሕአዴግ የተሻልኩ ነኝ ብሎ በአማራጭነት መቅረብና ለምርጫ መወዳደር ራስን ከገዢው ፓርቲ የላቀ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ገዢው ፓርቲ ጎሰኛ ነው እያሉ ጎሰኛ ሆኖ መገኘት፣ ከዚያኛው ጎሳ ቀብርና ሰርግ እንዳትሄዱ እያሉ በድርጅት ማህተም የተደገፈ መግለጫ ማሰራጨት ያሳፍራል፣ ሁሉም ተቃዋሚዎች እንደዚህ አይደሉም፡፡ ግን ነበሩ፣ አሉም፡፡ ከዚህ ፀድተው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፓርቲ መሆናቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡

6.    
ሁሌም ሰላማዊ ትግል እንጂ "ሲሞቅ በማንኪያ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ" መሆን የለበትም

በሰላማዊ ትግል ማመን ማለት ሌላው ይህንን መርህ ሲጥስም ማውገዝ ማለት ጭምር ነው፡፡ ዛሬ የትጥቅ ትግል ነገ ሰላማዊ ትግል እያሉ መሄድም ማለትም አይደለም፡፡ ሁሌም ሰላማዊ ትግል ማለት ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሰላማዊ ትግል ይፈቅዳል፡፡ መሆን ያለበትም እሱ ነው፡፡ የትጥቅ ትግል አካሂዳለሁ ማለት መሳሪያ በተመዘዘ ጊዜ ለመቃወም የሚያስቸግር በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ትግል በገዛ ራሱ ምክንያት ካለው ፋይዳ አኳያ ተቃዋሚዎች ለሰላማዊ ትግል ብቻ ይታዘዙ ዘንድ ይጠይቃል፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸው ትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ አይደሉም አያምኑበትምም ሌላ ሲያካሂድና አካሂዳለሁ ሲል ግን ማውገዙ ላይ የሉበትም፡፡ የትጥቅ ትግል የሚጎዳው ገዢውን ፓርቲና መንግስትን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ አገርን ነው፡፡

7.    
ራሳቸው መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ አይደሉም

ትግል መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ እስር ቤትና መታሰር ሊኖር እንደሚችል ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ትግል ከምቾት እንደሚያርቅ መታወቅ አለበት፡፡ አምኖ የተከተለን ሕዝብ ሳያከብሩ ከእሰር ቤት ወጥቶ ወደ ውጭ ሩጫ መጀመርም ያስተዛዝባል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ ሆኖ የትጥቅ ትግል ላይ ነን ይታወቅልን ማለትም "ጉድ እኮ ነው" የሚያሰኝ ነው፡፡ ትግል የሚፈልግ ሁሉ አገር ቤት ገብቶ የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍሎ ታጋይነቱን ማስመስከር አለበት፡፡ "ኢሕአዴግ ሲወድቅ ደውልልኝ" ብሎ መጠባበቅና ዋጋ ሳይከፍሉ "ኢሕአዴግን ከጣልክልኝ ወርቅ ዣንጥላ" ብሎ ስለት መግባት በቋሚነትም በጊዜያዊነትም ታጋይነትን አያሳይም፡፡

ያለው ድክመት ብዙ ነው፡፡ ድክመቱ ያለው በተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በገዢ ፓርቲም ጭምር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በኢሕአዴግ ላይ ስለፃፍን ነው ዛሬ በተቃዋሚዎች ላይ ትኩረት ያደረግነው፡፡-

ተቃዋሚዎች መጠናከር አለባቸው፡፡ ይችላሉም፡፡ አሁን ጀምረውም ለምርጫው ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ቀደም ብለን ያሰፈርናቸውን ሦስት ነጥቦች ሊያተኩሩባቸውና ሊያርሟቸው ይገባል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ ተቃዋሚ እንዲሆኑ በራሳቸው ድክመትና ጉድለት ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሊያሳዩ ይገባል፡፡

Last Updated ( Monday, 20 July 2009 )